በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አኃዱ አምላክ፤ አሜን።
ልደተ ክርስቶስ
የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ተላልፎ በሐጢያት ከወደቀ በኋላ እግዚአብሔር ወደ ቀደመ ክብሩና ቦታው ይመልሰው ዘንድ በንሰሐ ወደፈጣሪው ቀረበ። አዳም እና ሔዋን ከገነት ከወጡ በኋላ ለአርባ ቀናት ያህል ሱባዔ ገብተው ሳለ በ35 ኛው ቀን ከግማሽ ላይ ቀድሞ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ እንዲያፈርሱ ያደረጋቸው ሰይጣን ዳግመኛ ወደ ሔዋን ቀርቦ ሔዋን ሆይ ጸሎታችሁ ተሰማ አዳምን ይዘሽ ወደዚህ ነይ አላት። እርሷም በጎ መልአክ መስሎ የቀረበውን የጥንተ ጠላታቸውን ድምጽ ሰምታ አዳምን ይዛ ከሱባኤያቸው ወጡ። በመንገድም ሲሄዱ በጎ መልአክ መስሎ የመጣው ዲያብሎስ አሁን አገኘሁህ ከኔ አታመልጥም ብሎ አዳምን ድንጋይ አንስቶ ፈነከተውና ተሰወረ።
አዳምም በወደቀበት ደሙን እያዘራ ምርር ብሎ በማልቀስ ከዋለ ካደረ በኋላ እውነተኛው መልአክ ቅዱስ ገብረኤል ተገልጾ አጽናናው። ፈጣሪ አምላክም የደረሰበትን ሁሉ አይቶ አዘነለት። ከወደቀበት መከራም ሁሉ ያድነው ዘንድ ወዶ የተስፋ ቃል ሰጠው። ይህም የተስፋ ቃል ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ መጥቼ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው የሚል ነበረ።
መልአኩም ቅዱስ ገብርኤል በል ተነስተህ ሔዋንን ያዝና ሂድ ብሎ አዘዘው። አዳም ግን ይህች ሴት ሁለት ጊዜ ከፈጣሪዬ አጣላችኝ ከዚህ በኋላ ላያት አልፈልግም ብሎ እምቢ አለ። መላኩም አዳም ሆይ ከወጣህበት ገነት የምትመለሰው ድህነትንም የምታገኘው በእርሷ በኩል ነውና ሔዋንን ይዘህ ሂድ አለው። በዚህም ለሰዎች ድኅነትን የምታሰጥ የመድኃኒታቸው መገኛ የሆነች ዳግማዊት ሄዋን የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የድህነታች መሠረት እንደሆነች ታወቀ።
ዳግመኛም አምላክ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው ያለውን የተስፋ ቃል አዳም በልቡ ሰንቆ መኖሩ ያቺ የተስፋው ቃል ድንግል ማርያም እንደሆነች የተረዳ ነገር ሆነ። ሊቁ “አንቲሁ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት” በማለት እንደተናገረው ከገነት በተሰደደ ጊዜ ለአዳም ተስፋው የሆነች ድንግል ማርያም ናትና።
እንግዲህ ይህ የዘመን ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ የሰው ልጆችን ሊያድን ጌታችን እና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ።
ከመወልዱ አስቀድሞ ከተወለደም በኋላ በምን ሁኔታ እንደሚጸነስ እና የት፣ ከማን፣ እንደምን ባለ ሁኔታ እንደሚወለድ በአበውና በነብያት እንዲሁም በሃዋርያት መጽሐፍት ውስጥ ታርኩ በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል። ከእነኝህ የመጽሐፍት ክፍሎች ውስጥ አብዛኛውን ለአንባብያን በመተው ጥቂቶቹን ብቻ እንደሚከተለው እንመለከታለን።
ወዳጆች ሆይ፤ እኒህን ሁሉ የእግዚአብሔር ቃሎች አምነን የጌታን ልደት ስናከብር ድርሻችን ታሪኩን ማወቅና በእግዚአብሔር ልጅ ማመን ብቻ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወዚህ ዓለም የመጣበትን ዋነኛውን ዓላማ ፈጽመን እንድንገኝም ጭምር ነው። ይኽውም ከሃጢያትና በደል እርቀን ብርሃን የሆነንን ክርስቶስን ለብሰን ዘወትር ዝግጁ በመሆን የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ የበቃን እንድንሆን ነው። የጌታን ልደት የምናከብርበት የገና በአል ዘወትር በየአመቱ ሲመላለስ እኛም ዘወትር በንሰሐ እየታደስን በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ በመወሰን አዲስ ሕይወትና አዲስ መንፈስ ሊኖረን ይገባል። ነብዩ ““ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ለእናንተ አድርጉ :: ብሎ እንደነገረን ” ሕዝ. 18፥31
መልካም በአል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክብር።